በጎንደር ከተማ ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በግንባታ ላይ ናቸው

በጎንደር ከተማ ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በግንባታ ላይ ናቸው

በጎንደር ከተማ

ጎንደር ጥር 28/2011 በጎንደር ከተማ በዚህ ዓመት ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 21 ባለሃብቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ወደ ሥራ ይገባሉ የሚባሉት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ለ18 ሺህ ዜጎች ሥራ ይፈጥራሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ አለባቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ በተለያዩ የኢንዱስትሪ መስኮች በመሰማራት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት 21 ባለሃብቶች ናቸው።

ባለሀብቶቹ ግንባታውን የሚያካሂዱት በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ በኬሚካልና ከረጢት፣ በምግብ ነክ እንዲሁም በእንጨትና በብረታብረት ዘርፎች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ለ111 ዜጎች ቋሚና ለ550 ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ ሥራ መፍጠራቸውን አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።

በከተማው በተመሰረተው የኢንዱስትሪ መንደር ለሚካሄዱት ፕሮጀክቶች መሠረተ ልማት ተቋማት በመሟላት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ የብድር ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

”ተጨማሪ 53 ባለሃብቶች ፕሮጀክት ቀርፀው በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመሰማራት የጠየቁ ሲሆን፣ እነዚህን ባለሀብቶች ለማስተናገድ ከተማ አስተዳደሩ 50 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል” በማለትም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ለ18ሺህ ዜጎች ሥራ እንደሚፈጥሩና ስድስቱ በሚቀጥለው ዓመት ፣15ቱ ደግሞ በ2013 ሥራ እንደሚጀምሩ ኃላፊው አስረድተዋል።

በከተማው በኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ስንታየሁ ጌጡ በከተማው በ120 ሚሊዮን ብር ካፒታል የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመክፈት በግንባታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የፋብሪካው ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ200 ሰዎች በላይ ሥራ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ባለሀብቱ ሥራ ከፈጠሩላቸው መካከል ወጣት ሽባባው ደስታ በከተማው የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች እየፈጠሩ ባሉት ሥራ ዜጎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ ብሏል ፡፡

ሌላው በከተማዋ በምግብ ነክ የሥራ ዘርፍ ቅመማ ቅመም ማቀነባበር በግንባታ ላይ ያሉት አቶ ግርማ መንግሥቱ ለተረከቡት ቦታ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እንደተሰጣቸውና የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክታቸውም ለ34 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ፈጥሯል፡፡

በከተማው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያደገ ቢሆንም፤መሬት ከሶስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ፣ ባለሀብቶች ቦታ ከወሰዱ በኋላ ፈጥኖ ወደ ሥራ ያለመግባትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግሮች እንደሚታዩ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ [ENA]

C and E brothers steel factory
size-165-x-620-px
error: Content is protected !!